አለም አቀፍ የሴቶች ቀን 'ማርች 8' ተከበረ
የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግ እና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ይረዳ ዘንድ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 በየዓመቱ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል፡፡ የዘንድሮው በዓል 'እኩልነት ለላቀ እድገት' በሚል መሪ ቃል የአመልድ ሰራተኞችና ሃላፊዎች በተገኙበት በስርዓተ-ፆታ ባህል እና አካል ጉዳት አገልግሎት ክፍል አዘጋጅነት በቀን 29/06/2011 ዓ.ም ተከብሯል፡፡
በዓሉን በንግግር የከፈቱት የአመልድ ዋና ዳሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ እንዳሉት፤በተለያዩ ጎጂ ልማዶች እና አስተሳሰቦች ምክንያት ሴቶችን እኩል በማህበራዊ፣ በፖለቲካ እና ኢኮኖሚው ዘርፍ ባላማሳተፋችን ኢትዮጵያ ግመሽ የሰው ሃይሏ እየተጠቀመች አይደለም ፤ይልቁንም ሴት ልጆች በቤት ውስጥ የስራ ጫና ስለሚበዛባቸው ከወንዶች እኩል ተሳትፎ እንዳያደርጉ ማነቆ ሁኗል፡፡ እስካንዴኒቪያን አገሮች በሴቶች እኩልነት እና ተሳትፎ የተሻሉ በመሆናቸው በአጠቃላይ እድገት የተሻሉ ናቸው ሲሉ በኢትዮጽያ የሴቶች በኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ዘርፍ እኩል ተሳታፊ ስላልሆኑ ማደግ የሚገባንን ያህል አላደግንም ብለዋል፡፡ እንደአመልድ በቀጣይ ሰፊ የልምድ ልውውጦች በሰራተኛው መካከል እንደሚደረግ አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ የግንዛቤ መስጫ ፅሁፎች ከቀረበ በኋላ፤ በቤት ውስጥ በስርዓተ -ፆታ እኩልነት፣ የቤት ውስጥ የስራ ድርሻ ክፍፍል እና ውሳኔ ሰጭነት ላይ ተሞክሮ ያላቸው ሰራተኞች ልምዳቸውን አካፍለዋል፡፡ እንዲሁም በእለቱ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የጥያቄ እና መልስ ውድድር ተደርጎ ለአሸናፊዎች ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ በቀጣይ በስርዓተ-ፆታ ጉዳይ የሚያተኩሩ ሰፊ ውይይቶች እና ስልጠናዎች እንደሚሰጡ በመድረኩ መዝጊያ ላይ ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ ተናግረዋል፡፡