አመልድ ኢትዮጵያ በ2015/ 2016 ዓ.ም በአማራ እና በአፋር ክልል 6.5 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት በ134 ወረዳዎች 38 ፕሮጀክቶች እንደሚተገበር ተገለጸ፡፡
አመልድ ኢትዮጵያ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ ስር የሰደደውን ድህነት እና ረሃብ ለማስወገድ ስትራቴጅ ነድፎ እየሰራ ይገኛል፡፡ የደርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዓለማየሁ ዋሴ (ፒኤች.ዲ) ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ "እ.ኤ.አ በ2023 በአማራ ክልል እና በአፋር ክልል በጠቅላላ 38 ፕሮጀክቶች ይተገበራሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 31 ፕሮጀክቶች ከባለፈው ዓመት የቀጠሉ ሲሆኑ 7 ፕሮጀክቶች ግን በአዲስ የሚከፈቱ ናቸው፡፡ በ134 ወረዳዎች በአማራ እና አፋር ክልል ላይ እንሰማራለን፡፡ በ71 ወረዳዎች የልማት ስራ እንሰራለን፤ በ98 ወረዳዎች ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ በአጠቃላይ እ.ኤ.አ በ2023 ለማንቀሳቀስ ያሰብነው 6.5 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት ነው" ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው እስካሁን ለማህበረሰብ ልማት ድጋፍ ያደረጉ ለጋሾችን አመስግነው በቀጣይም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
"የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የአካባቢው ህብረተሰብ ከዚህ በፊት እንደሚያደርገው አመልድ ኢትዮጵያ የራሴ ድርጅት ነው የሚሉት፡፡ ንብረቶችን ይጠብቃል፣ አላስፈላጊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ሪፖርት ያደርጋል፣እኛ ምንሰጣቸው ድጋፍ ደግሞ መነሻ እንጅ መጨረሻ እንዳልሆነ ያውቃሉ፤ስለዚህ እኛ በምናደርገው ድጋፍ ተነስተው ወደ ተሻለ ኑሮ እንዲመጡ እስካሁን የሚያደርጉትን ትብብር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በአካባቢው ያሉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አመልድ ኢትዮጵያን እንደራሳቸው የበጀት አካል አድርገው ክትትል እንዲያደርጉ በዚህ አጋጣሚ ጥሪየን አቀርባለሁ፡፡ እንደዚሁም ከእኛ ጋር አብረውን የሚሰሩ እምነት የጣሉብን አለም አቀፍ ድርጅቶች እስካሁን ለሰጡን ድጋፍ እና እምነታቸውን በእኛ ላይ ስለጣሉ፣ ወደፊትም አብረውን ስለሚሰሩ እናመሰግናለን" ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ፡፡