Joomla TemplatesBest Web HostingBest Joomla Hosting

ዋና ገፅ ዜና አጫጭር ዜናዎች የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) የ4ኛውን የኢትየጵያ ጥራት ሽልማት ውድድር በአንደኝነት አጠናቀቀ

የፕረስ ሪልዝ

የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) የ4ኛውን የኢትየጵያ ጥራት ሽልማት ውድድር በአንደኝነት አጠናቀቀ

የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) የ4ኛውን የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ውድድር ከሁሉም ተወዳዳሪ ድርጅቶች የበለጠ ውጤት በማስመዝገብ አሸነፈ፡፡

ይህ የተገለፀው በሰኔ 10/2008 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል በተካሄደው የአራተኛው የኢትዮጵያ ሽልማት አሰጣጥ ስነስርዓት ላይ ነው፡፡ በዚሁ ስነስርኣትም ላይ ድርጅታችን አመልድ ያገኘውን የአንደኛነት ደረጃ ዋንጫና የምስክር ወረቀት የድርጅታችን ዋና ዳይሬክተር ክቡር ዶ/ር አምላኩ አስረስ ከክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት እጅ ተቀብለዋል፡፡

              Dr Amelaku & DR mulatu

የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት በአማራ ክልል የበለፀገ ማህበረሰብ እንዲፈጠር ከመንግስትና ከህዝቡ ጎን በመሆን ለአለፉት 32 ዓመታት የራሱን ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ መንግስታዊ ያልሆነ የበጎ አድራጎትና የልማት ድርጅት ነው፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ የእርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት (አዕማድ) የአሁኑ አመልድ የዛሬ 32 ዓመታት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ደርሶ በነበረው አስከፊ ድርቅና ረሃብ ምክንያት ከፍተኛ አደጋ ተጋርጦባቸው የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለመታደግ ተብሎ በኢህዴን/ብአዴን ታጋዮች የተቋቋመ ድርጀርት ነው፡፡ በዚያ ወቅት አመልድ ኢትዮጵያ ዉስጥ ቢሮ ከፍቶ ለመስራት የሚያስችለው ሁኔታ ስላልነበር በሱዳን ካርቱምና ገዳሪፍ  ቢሮ በመከፈት ከአለም አቀፍ የረጅ ድርጅቶች የሚያገኘውን ምግብ፣ ገንዘብና መድሃኒት በሰውና በጋማ ከብቶች ወደ ኢትዮጵያ በማጓጓዝና ለተጎጅ ህብረተሰቦች በማዳረስ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ከረሀብና ከሞ በመታደግ ታሪክ የማይረሳው ገድል የፈፀመ ድርጅት ነው፡፡

1983 ዓ.ም ላይ ደግሞ በሃገራችን የተከሰተውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ድርጅታችን አመልድ ቢሮውን በባህርዳር ከተማ ከፍቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ እስከ 1989 ዓ.ም ድረስም በርካታ የዕለት ዕርዳታና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በመስራት በጦርነት፣ በረሃብና በስደት ምክንያት ተጎድተው የነበሩ የክልላችንና የሃገራችን ህዝቦች መልሶ የማቋቋም ስራዎችን በአግባቡ አከናውኗል፡፡

የድርጅታችን ትኩረት መስክ “ከዕለት ዕርዳታ” ወደ “ልማት” ከተሸጋገረበት ከ 1989 ዓ.ም ወዲህ ደግሞ የአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ ከሚያደርጉት ርብርብ ጎን በመሰለፍ ሶስት የአምስት አመታት ስትራቴጅካዊ ዕቅዶችን በመፈፀም በልማቱ መስክም ሰፊ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ ከነዚህ ከተገኙ ድሎች መካከልም የሚከተሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ከክልላችን የደን ሽፋን ውስጥ 8 በመቶውን ከህዝቡ ጋር በመሆን እንዲለማ አድርጓል፡፡ ከክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋን ውስጥ 18 በመቶው በአመልድ የተሰራ ነው፡፡ ከክልላችን በዘመናዊ መስኖ ከሚለማው መሬት 10 በመቶው የሚሆነው እየለማ ያለው በአመልድ በተሰሩ መስኖዎች ነው፡፡ ከ500 ሽህ በላይ ለሚሆኑ የክልላችን ህዝቦች ዕውቀት፣ ግብአትና ቴክኖሎጅዎችን በማቅረብ እንዲጠቀሙና ከምግብ ዋስትና ችግር እንዲላቀቁ ተከታታይ ስራ እየሰራ ነው፡፡ አመልድ በሚሰራባቸው ቤተሰቦችና አካባቢዎች የተዛባ የስርዓተ ፆታ ግንኙነት እንዲስተካከልና የፆታ እኩልነት እንዲረጋገጥ አድርጓል፡፡  በአለፉት ሁለት አመታትም አዲስ መርሃግብር መበክፈት  ከ6000 ያላነሱ የክልላችን ስራ አጥ ወጣቶች ቋሚ የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ አመልድ እነዚህንና መሰል የልማት ድሎችን በማስመዝገብ የክለሉ ህዝብና መንግስት የልማት አጋርነቱን በተግባር ያረጋገጠ ድርጅት ለመሆን በቅቷል፡፡ ድርጅታችን አመልድ እነዚህን ድሎች ማስመዝገብ የቻለውም ለጥራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መላ ሠራተኞችን ባሳተፈ መልኩ ርብርብ ስላደረገ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅትም ይህን የድርጅታችንን ዙሪያ መለስ ጥረትና ድሎች በአግባቡ በመመርመር ለአራተኛው የጥራት ሽልማት ድርጅታችን በአንደኝነት ደረጃ እንዲሰሸለም ማድረጉ እነዚህን ከአንድ ህዝባዊና ጠንካራ የበጎ አድራጎት ድርጅት ብቻ ሊገኙ የሚችሉ ድሎችን በማረጋገጡ ብቻ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ አድካሚ የነበረውን የድርጅታችንን አጠቃላይ ሁኔታ የመፈተሸ ስራ በአግባቡ ሰርቶ ለዚህ ታላቅ የሆነ ሽልማት ብቁ ናችሁ ብሎ እንድንሸለም ላደረገን የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድረጅትና በስሩ በተለያየ አደረጃጀት በበጎ ፈቃደኝነት ለሰሩ ዳኞችና የቴክኒክ ኮሚቴዎች ያለንን አድናቆት መግለፅ እንፈልጋለን፡፡

              orda

በመጨረሻም የድርጅታችን የቦርድ አባላት፣ አመራር አባላት፣ መላው ሠራተኞች፣ የመንግስት አጋሮች፣ ረጅ ድርጅቶችና ህዝቡ ይህ ድርጅታችን ያገኘው ክብር ካለናንተ የነቃ ተሳትፎና ድጋፍ ሊሳካ ቀርቶ ሊታሰብ የሚችል አልነበረምና፤ እንዲሁም የድርጅታችን ድል የእናንተም ስለሆነ ደስታችን ደስታችሁ ነውና እንኳንም ደስ ያላችሁ ማለት እንወዳለን፡፡

ይህ ዛሬ ያገኘነው ሽልማት ደግሞ “የበለፀገ የአማራ ክልል ህዝብ” ለማየት ያለንን ራዕይ ለማሳካት የፕሮግራም አፈፃፀም ጥራትን ይበልጥ ለማሻሻልና የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያነሳሳን በመሆኑ ከምንጊዜውም የበለጠ ተግተን እንደምንሠራ በዚህ አጋጣሚ እናረጋግጣለን፡፡

የአመልድ ኮሙኒኬሽንና የመረጃ ቴክኖሎጅ የስራ ክፍል፡፡

 
ቋንቋ
ሶሻል ሚዲያ
FacebookTwitter
የጎብኝዎች ብዛት
Today48
Week114
All72158

Currently are 15 guests online


ምርጫ
ስለ ድረ-ገፅ ያለዎት አስተያየት ?