Joomla TemplatesBest Web HostingBest Joomla Hosting

ዋና ገፅ

                            ዋና ዳይሬክተር መልዕክት

DrAlemayehu

በድርጅታችን ድረ-ገጽ መልዕክቴን ሳስተልፍ ክብርና ደስታ ይሰማኛል፡፡ እንዲሁም በዚህ አጋጣሚ የአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለነበራችሁ የመንግስት፣ የግልና የሶስተኛው ሴክተር አካላት ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ በአለፉት 32 ዓመታት የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ዘላቂ የኑሮ ለውጥና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎችን በመስራት የድህነትን መሰረታዊ ምንጭና የማህበረሰቦችን ለተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ተጋላጭነት ችግር ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡

አመልድ በአሁኑ ወቅት 1.96 ሚሊዮን የሚሆኑ ህዝቦችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ለመቅረፍ የሚያግዙ የተቀናጁ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያና ልማት ፕሮግራሞችን በ60 የአማራ ክልል ወረዳዎች ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ አመልድ በተፈጥሮ ሃብት ልማት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የአካባቢና የግል ንፅህናና በመስኖ ልማት፣ በምግብ ዋስትናና በግብርና ልማት እንዲሁም በወጣቶች ስራ ፈጠራ ላይ የሚያተኩሩ 4 ዋና ዋና ፕሮግራሞች አሉት፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች ስራዎቻቸውን ሲፈፀሙ የስርአተ-ፆታ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የአደጋ ተጋላጭነትን መቀነስ፣ የአካባቢ ለውጥ መቋቋም የመሳሰሉ ስራዎችን ከዋነኛ ስራዎቻቸው ጋር በጥብቅ አካተው እንዲፈፅሙ ይደረጋል፡፡ በአራቱ ፕሮግራሞች ስር የሚከተሉት ተግባራት ይፈፀማሉ፡- የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት፣ ደን ልማት፣ ብዝሃ ህይወት እንክብካቤ፣ አማራጭ የሃይል ምንጭ፣ ንፁህ የመጠጥ ውሃና የግልና የአካባቢ ንፅህና (ዋሽ)፣ የመስኖ ልማት፣ የሰብልና የእንስሳት ሃብት ልማት፣ የፍርፍሬና አትክልት ልማት፣ የእሴት ሰንሰለትና የገበያ ልማት፣ግብርና ነክና ግብርና ነክ ያልሆኑ የገቢ ማስገኛ ስራዎች፣ ስርዓተ- ምግብ እና ለአነስተኛ መሬት ባለቤት አርሶ አደሮች ተስማሚ የሆኑ ምርታማ ቴክኖሎዎጅችን ማስተዋወቅና ማሰራጨት፡፡

ባለፉት አንድ ዓመት ከግማሽ ወራት (እ.ኤ.አ 2014/15) ከአካባቢ ብክለት የፀዳ ዘላቂ የኑሮ መሻሻል ማምጣት፣ ስትራቴጅካዊ አጋርነት ማጠናከርና የአፈፃጸም ልህቀት ማረጋገጥ በማለት የሚታወቁትን ሶስቱን የድርጅታችንን ስትራቴጂካዊ ግቦች  ለመሳካት የሚያስችል የተቋም መልሶ ማደራጀት ጥረትን ስመራ ቆይቻለሁ፡፡  

የመጀመሪያው ስትራቴጅካዊ ግብ የተለጠጠና አመልድ ከዕለት ደራሽ ዕርዳታ ወደ ዘላቂ ልማት ስራዎች የአቅጣጫ ለውጥ ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ ባለፉት 2 ዓመታት ያመጣቸውን በርካታ አዎንታዊ ውጤቶችን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ የአመልድ ቀዳሚ መለያ በሆነው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ፕሮግራም ስራዎች ምክንያትም ከክልላችን የደን ሽፋን ዉስጥ 8% የሚሆነዉን ድርጅታችን አስተዋፅኦ ከማድረጉ በላይ ለዚሁ አንፀባራቂ ውጤታችን እ.ኤ.አ የ2007 አገር አቀፍ የአረንጓዴ ጀግና ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ድርጅታችን ከክልላችን የውሃ ሽፋን ዉስጥ 18% አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ለዚሁ አብረቅራቂ ውጤቱም እ.ኤአ. በ2009 በአገር አቀፍ ደረጃ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ እንዲሁም 14¸ 201 ሄ/ር መሬትን ማልማት የሚችሉ 202 አነስተኛ የመስኖ ተቋማትን በመገንባት 70 ሺህ አባወራና እማዎራዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ከክልሉ የመስኖ ሽፋን ዉስጥ 5 በመቶ አስተዋፅኦ በማድረግ ለአየር ለውጥ የማይበገር ግብርና በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ በምግብ ዋስትናና በግብርና ልማት ፕሮግራም የተሻሻሉ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የእንስሳት ዝርያዎችን በማስተዋቅና በማስፋፋት፣ የገበያና የገቢ ማስገኛ ስራ አማራጮችን በማቅረብ ከ2.5 ሚሊዮን የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ሰዎች መካከል 20 በመቶ ማለትም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የክልላችንን ህዝቦች ተጠቃሚ እያደረግን ነው፡፡ ግብርና ነክ/-ያልሆኑና ከግብርና ውጭ ባሉ አማራጮች በመጠቀም 6¸000 የሚሆኑ ገቢ ማግኛ ስራዎች ለወጣቶች ተፈጥረዋል፡፡

 

ዘላቂ አጋርነት የሚለው ሁለተኛዉ የስትራቴጅክ ግብ በዘላቂ የልማት ሃብት አሰባሰብና አጠቃቀም ላይ ያተኩራል፡፡ በዚህ ረገድ በአለፉት አንድ አመት ከግማሽ (እ.ኤ.አ 2014/15) ባሉት የስትራቴጅክ ዘመን ጊዜያት ውስጥ 650 ሚሊዮን ብር አማካይ አመታዊ የልማት ሃብት ማሰባሰብ ችለናል፡፡ በአሁኑ ሰዓት አመልድ ከ29 የልማት አጋሮች ጋር በመሆን 56 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በ60 የክልሉ ወረዳዎች ውስጥ እየተገበረ ይገኛል፡፡

 

ሶስተኛው የስትራቴጅክ ግብ ማለትም የአፈፃፀም ልህቀት ማረጋገጥ የሚያተኩረው በስርአት መዘርጋትና ተግባራዊ ማድረግ ላይ ነዉ፡፡ ስትራቴጅዉን ተግባራዊ ለማድረግ በአግባቡ የተደራጀ የተቋማዊ አቅም ዳሰሳ ተደርጓል፡፡ በዳሰሳዉም ለድርጅቱ መጠንከር የሚጠቅሙ መዋቅራዊ፣ ፖሊሲ ነክ፣ የአሰራር ስርዓቶችና ሂደቶችን የሚመለከቱ ክፍተቶችን መለየት ተችሏል፡፡ ይህን መሰረት በማድረግ የአቅም ግንባታ የድርጊት መርሃግብር ተዘጋጅቶ ተግባራዊም በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡

 

ራዕያችን “የበለፀገ የአማራ ክልል ህዝብ ማየት” ነው፡፡ ራዕያችንን ዕውን ለማድረግ ሁለት ነገሮች በጣም ወሳኝ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጉዳይ የፕሮግራም ጥራትን ማስጠበቅ ነው፡፡ የፕሮግራም ጥራት ስንል የምንተገብራቸው መፍትሄዎች ካጋጠሙን ችግሮቻችን ጋር ምን ያህል ተመጣጣኝ ናቸው የሚለውን የሚመለከት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የገጠመንን ችግር በውል ተረድተነዋል ወይ? ለችግሩ መፍቻስ ያስቀመጥነው መልስ ችግሩን የሚፈታ ነው ወይ? መፍትሄው እንዴት እንደሚተገበር የሚያውቅ ሰውስ ከአመልድ ውስጥም ሆነ ከአመልድ ውጭ አለ ወይ? ይህንስ መፍትሄ መጨበጥ ፣ መተግበርና ወደ ሌላ ተመሳሳይ ሁኔታና ችግር ውስጥ ባለ ቦታስ ወስደን ልናሰፋው እንችላለን ወይ? ተግባሮቻችን እነዚህን ወሳኝ ጥያቄዎችን መመለስ ላይ ማተኮር አለባቸው፡፡ ሁለተኛ ልማትን ለማረጋገጥ   የሚያስፈልጉን ወሳኝ ጉዳዮች የልማት ሃብትን በቁጠባ መጠቀም፣ በየደረጃው ካሉ መንግስት መዋቅሮች ጋር ውጤታማ የሆነ ግንኙነት መፍጠርን፣ የማህበረሰቡን ወሳኝ ማድረግና ተጠያቂነትን ማረጋጥ ናቸው፡፡

 

አመልድ በአሁኑ ጊዜ ድህነትንና የሚያስከትላቸውን ተጽዕኖዎች ለማስወገድ ሙሉ በሙሉ እየታገለ ይገኛል፡፡ እዉነቱን ለመናገር በዋናው መስሪያ ቤትም ሆነ በየፕሮጀክቶቻችን ያለን የአመልድ ሰራተኞ በየቀኑ ለማድረግ እየሞከርነው ያለው ይህንኑ ነው፡፡ በትብብር ተጨባጭ የልማት ለውጥ ለማምጣት ድርጅታችን ውስጥ በማየው ቆራጥነት ኩራት ይሰማኛል፡፡ በአገራችን የተንሰራፋው ድህነት ሙሉ በሙሉ እስካልተወገደ ድረስ እረፍት የለንም፡፡

 

በመጨረሻም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የልማት ሃብት በመለገስ እየደገፉን ያሉ የልማት አጋሮችን እያመሰገንሁ ወደፊትም ይህንኑ ለአማራ ክልል ህዝብ የሚያደርጉትን ያላሰለሰ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ እጠይቃለሁ፡፡ ለመንግስት አጋሮቻችንንም እንዲሁ አመሰግናለሁ፡፡ እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብታችንን በማልማትና በመንከባከብ፣ ሁሉም የክልሉ ነዋሪዎች በቂና ንፁህ ውሃ ለመጠጥና ለመስኖ እንዲያገኙ፣የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል እና ለወጣቶች ስራ ለመፍጠር የሚደረገውን ክልላዊ ጥረት በመደገፍ የጋራ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት በከፍተኛ ቆራጥነት እየተንቀሳቀሱ ያሉትን የአመልድ ሰራተኞችን ማድነቅ እወዳለሁ፡፡  እንዲህ ስናደርግ የጋራ ሃብታችን ይጨምራል የሰው ልጆች ህይወትም ይበለጽጋል፡፡ የምኮራባችሁ አመልድ ውስጥ ያላችሁ የስራ ባልደረቦቼ አሁንም ቢሆን የድርጅታችንን ተልዕኮ ለማሳካት ይበልጥ እንንቀሳቀስ እላለሁ፡፡ ይህ ትውልድ ፍፁም ድህነትንና የኢኮኖሚ ኢ-ፍትሃዊ ክፍፍል ከክልላችን የሚያጠፋ ትውልድ እንዲሆን እንስራ፡፡ በጋራ ድህነትን ታሪክ እናደርጋለን!!

 

መጪ ጊዜ የክልላችን ብሎም የአገራችን ኢትዮጵያ ብልጽግና ዕውን የሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡

Last Updated (Friday, 15 February 2019 07:36)

Read more...